ፈልግ

በሳና ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የአየር ድብደባ ከደረሰ በኋላ የተከሰተ ጭስ በሳና ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ላይ የአየር ድብደባ ከደረሰ በኋላ የተከሰተ ጭስ  (REUTERS)

ኢራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን በመዝጋቷ አሜሪካ አዲስ ጥቃት መሰንዘሯ ተገለጸ

የኢራን ኃይሎች የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥን በመሻገር ላይ የነበረውን መርከብ መምታታቸውን ተከትሎ አሜሪካ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት መሰንዘሯ ተገለጸ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

አሜሪካ የኢራን ኃይሎች የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ አቋርጦ በማለፍ ላይ የነበረውን መርከብ በመምታታቸው ምክንያት አዲስ ጥቃት መፈጸሟ የተነገረ ሲሆን፥ የኢራን ቴሌቪዥን በበኩሉ በሃገሪቱ በርካታ ክፍሎች ጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጿል።

አሜሪካ ቅዳሜ እና እሁድ በፈጸመችው ጥቃት 140 የሚያህሉ የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎችን መመታታቸውን ከክልሉ የሚወጡ ዘገባዎች የሚያመለክቱ ሲሆን፥ እነዚህ ጥቃቶች የሚሳኤል እና የድሮን ጣቢያዎችን፣ የመገናኛ አውታረ መረቦችን እና የባህር ዳርቻ የክትትል ቦታዎችን እንደሚያካትቱ ተገልጿል።

እሁድ ዕለት የኢራን ጦር የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ “ላልተወሰነ ጊዜ” እንደተዘጋ ማሳወቁ የተነገረ ሲሆን፥ ኢራን በአሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና ተባባሪ ሀገራት ላይ ጥቃት መፈጽሟን እና በዮርዳኖስ የሚገኘውን የአሜሪካን ጦር ሰፈር መምታቷን ስትገልጽ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ኩዌት እና ባህሬን የኢራንን ሚሳኤሎች እና ድሮኖች ማክሸፋቸውን ይፋ አድርገዋል።

ይሄንን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የገቡት ጦርነት ከሰኔ 30 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ዳግም መቀጠሉን ለኮንግረስ በደብዳቤ ማሳወቃቸው ተገልጿል።

ዋሽንግተን ቅዳሜ ዕለት ቴህራን የባህር ወሽመጥ ክፍት መሆኑን በይፋ እንድታረጋግጥ እና በንግድ መርከቦች ላይ የምታደርገውን ጥቃት እንድታቆም ማሳሰቧ ይታወሳል።

በባሕረ ሰላጤው የሚገኙት ዮርዳኖስ እና ባሕሬን በግዛታቸው ውስጥ ጥቃት እንደተፈፀመባቸው የገለጹ ሲሆን፥ ኢራን ጥቃቱ የፈፀመችው የአሜሪካ ጥቃት ለሦስተኛ ቀን ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት እንደሆነ ተገልጿል።

የባሕሬን የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ሌሊት በተለያየ ሰዓት ሦስት ማስጠንቀቂያዎችን በማሰማት ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ወደሚገኝ መጠለያ እንዲገቡ ያስጠነቀቀ ሲሆን፥ የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ ዘብም በአገሪቷ አሜሪካ የምትገለገልበትን የተለያዩ ሥፍራዎች ዒላማ ማድረጉን ገልጿል።

የአሜሪካ ሚዲያዎች የኢራን ባለስልጣናት ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪዎች የመርከብ ጥቃቶቹ በአጭበርባሪ አንጃዎች በስህተት የተፈፀሙ መሆናቸውን በግል እንደገለጹላቸው ይፋ ያደረጉ ሲሆን፥ ሁለቱ ሃገራት ሰኔ ወር ላይ ለንግድ መርከቦች ደህንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ እንዲያገኙ ዋስትና የሚሰጥ የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ጋዛ ያለው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ
በሌላ ዜና የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት፣ የህክምና ቁሳቁስ እና የአምቡላንስ አገልግሎቶች እጥረት መኖሩንን በመጥቀስ እየተባባሰ የመጣ የሕክምና ድንገተኛ አደጋ እንደሚከሰት አስጠንቅቀዋል።

የህክምና እርዳታ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት መሐመድ አቡ አፋሽ እንደተናገሩት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ በተገባላቸው የተስፋ ቃል መሰረት የህክምና ቁሳቁሶችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዳልደረሱ ገልጸው፥ ይህም እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት እንዲከሰት ማድረጉን እና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ታካሚዎችን ለመርዳት አዳጋች ማድረጉን አስረድተዋል።

14 Jul 2026, 15:37