የታኅሣሥ 05/2018 ዓ.ም ዘአስተምህሮ 5ኛ እለተ ሰንበት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. 1ቆሮ 15፡12-32
2. 2ጴጥሮስ 3፡10-18
3. ሐዋርያት 20፡28-38
4. ሉቃስ 12፡32-40
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል
በምድር ላይ ሀብት ማከማቸት እንደማይገባ
“አንተ ታናሽ መንጋ! መንግሥትን ሊሰጣችሁ የአባታችሁ በጎ ፈቃድ ነውና አትፍሩ። ያላችሁን ሽጡ፤ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ፤ መዝገባችሁ ባለበት ልባችሁ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።
ትጉህ አገልጋዮች
“ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፤ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ፤ ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ከሌሊቱም በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንዲሁ ቢያገኛቸው፥ እነዚያ ባርያዎች ብፁዓን ናቸው። ይህን ግን እወቁ ባለቤት በምን ሰዓት ሌባ እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ፥ ቤቱም እንዲቆፈር ባልፈቀደም ነበር። እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።”
ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ! ይህን ምሳሌ ለእኛ ወይስ ደግሞ ለሁሉ ትናገራለህን?” አለው። ጌታም አለ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና ልባም መጋቢ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባርያ ብፁዕ ነው። እውነት እላችኋለሁ፤ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል። ያ ባርያ ግን ‘ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል’ ብሎ በልቡ ቢያስብ ሎሌዎችንና ገረዶችንም ይመታ ይበላም ይጠጣም ይሰክርም ዘንድ ቢጀምር፥ የዚያ ባርያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፤ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፤ እድሉንም ከማይታመኑ ጋር ያደርጋል። የጌታውንም ፈቃድ አውቆ ያልተዘጋጀ እንደሱም ፈቃድ ያላደረገ ያ ባርያ እጅግ ይገረፋል ያላወቀ ግን መገረፍ የሚገባውንም ያደረገ ጥቂት ይገረፋል። ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፤ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!
በዛሬው የመጀመርያው የስብከተ ገና ሣምንት ላይ የተነበበው የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ውስጥ (ሉቃስ 12፡32-48 ይመልከቱ) ኢየሱስ ደቀ-መዛሙርቱን በቋሚነት ነቅተው ይጠብቁ ዘንድ ያሳስባቸዋል። ለምን? በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን ጉዞ ለመረዳት ይቻል ዘንድ ነው፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ያለማቋረጥ ወደ ሕይወታችን ውስጥ ይገባል። እናም ነቅተን ለመኖር የምንችልባቸውን መንገዶች በማሳየት “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ፤ መብራታችሁም የበራ ይሁን” (ሉቃስ 12፡35) ይለናል። ይህ ቅድመ ሁኔታ ነው። በመጀመሪያ “በአጭር ታጥቃችሁ ተዘጋጁ” የሚለው ሐረግ በራሱ ለጉዞ የሚደረገውን ዝግጅት የሚያመለክት ሲሆን በአጠቃላይ ጉዞ ለማደረግ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅን ያመለክታል። ምቾት በሚሰጡን ነገሮች እና ደህንነታችንን በሚያረጋግጡ ምቹ በሆኑ ግንቦች ውስጥ ተከልሎ መኖር እና ሥር መሰረታችንን በእነዚህ ነገሮች ላይ እንዳናደርግ የሚያሳስበን ሲሆን ነገር ግን ከእነዚህ ነገሮች ተላቀን በሕይወታችን ውስጥ ወደሚቀጥለው እግዚአብሔር ወደ ሚመራን ግብ በመራመድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመፈጸም፣ እግዚኣብሔር በሕይወታችን ውስጥ ይመላለስ ዘንድ በእምነት እና በትህትና ራሳችንን ለእርሱ ክፍት ማደረግ ማለት ነው። በዚህ አስቸጋሪ የሕይወት ጉዞ ውስጥ ስህተት እንዳንሥራ ጌታ ሁል ጊዜ እጃችንን በመያዝ ከእኛ ጋር አብሮ ይጓዛል። በእውነቱ ፣ በእግዚአብሄር የሚታመኑ ሰዎች የእምነት ሕይወት እንዲሁ ዝም ብሎ ቀጥ ብሎ የቆመ ነገር ሳይሆን ተንቀሳቃሽ የሆነ ነገር መሆኑን ይረዱታል። የእምነት ሕይወት-ጌታ ራሱ በየቀኑ ወደ ሚያመለክተው ወደ አዳዲስ ደረጃዎች የሚወስድ ቀጣይ ጉዞ ነው። ምክንያቱም እርሱ አስገራሚ፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጽም፣ እውነተኛ የሆኑ አዳዲስ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ እንዲከሰቱ የሚያደረግ ጌታ ነው።
በቀዳሚነት የነበረው ቅድመ ሁኔታ “በአጭሩ ታጥቃችሁ ጠብቁ” የሚለው ሲሆን ከእዚያ በመቀጠል ደግሞ የሌሊት ጨለማን ማብራት ይቻል ዘንድ “መብራትችሁ የበራ ይሁን” ይለናል። የሕይወትን “ሌሊቶች” ብርሃን ማብራት የሚችል እውነተኛ እና የበሰለ እምነት እንዲኖር ተጋብዘናል። ሁላችንም ብንሆን በሕይወት ሂደታችን ውስጥ የጨለሙብን መንፈሳዊ ሕይወት እንደ ነበረ እናውቃለን። የእምነት አምፖሎቻችንን ለማብራት እንችል ዘንድ ከኢየሱስ ጋር ከልብ በመጸለይ እና ቃሉን በማዳመጥ ሕይወታችንን በእምነት ብርሃን ሁል ጊዜ መመገብ ይጠይቃል። ከእዚህ ቀደም ብዙን ጊዜ ደጋግሜ የተናገርኩትን አንድ ነገር ዛሬም ቢሆን በድጋሚ ለማንሳት እፈልጋለሁ፣ አንዲት ትንሽ የሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ሁልጊዜ በኪሳችሁ እና በቦርሳችሁ ውስጥ አድርጋችሁ በመሄድ አንብቡት። ይህም ከኢየሱስ እና ከቃሉ ጋር ቀጣይነት ባለው መልኩ እንድትገናኙ ይረዳችኋል። በጸሎት እና መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘ ይህ መብራት ለሁሉም ሰዎች መልካም አገልግሎት ይሆን ዘንድ እንድናውለው በአደራ ተሰጥቶናል፣ ስለሆነም ማንም ሰው የራሱን ድነት ብቻ በእርግጠኝነት አይመለከትም፣ የሌሎች ሰዎችን ድነት ጭምር የመለከታል። አንድ ሰው የራሱን ውስጥ ብቻ በራሱ ኃይል ማብራት ይችላል ብሎ ማመን በራሱ ቅዤት ነው። እውነተኛ እመንት ራሱን ለሌሎች ክፍት ያደርጋል፣ ከወንድሞቹ ጋር መልካም የሆነ ሕበረት ይፈጥራል፣ በተለይም ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነትን መፍጠር ያለመክታል። እናም ኢየሱስ ይህንን አመለካከት በሚገባ እንድንገነዘብ ለማድረግ ከሠርጉ ሲመለስ የጌታውን መምጣት የሚጠባበቁትን አገልጋዮች ምሳሌ (ሉቃስ 12፡36-40) በመናገር ነቅተን የምንጠብቀበትን ሌላ መንገድ በመጠቆም፣ በመጨረሻው ቀን ከጌታ ጋር ለመገናኘት በምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን መጠበቅ እንደ ሚገባን ያመለክታል። እያንዳንዳችን በእዚያ የመጨረሻ ቀን ከእርሱ ጋር ፊት ለፊት መገናኘታችን አይቀሬ ነው። እያንዳንዳችን በመጨረሻው ቀን ከኢየሱስ ጋር የምንገኛኝበት ቁርጥ ቀን እንዳለን መዘንጋት አይኖርብንም። ኢየሱስ “ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል። ከሌሊቱ በሁለተኛውም ሆነ በሦስተኛው ክፍል መጥቶ እንደዚያው ነቅተው ቢያገኛቸው፣ እነዚያ አገልጋዮች ብፁዓን ናቸው” (ሉቃ 1፡37-38) በማለት ይናገራል። በእነዚህ ቃላት ጌታ ሕይወት ወደ ዘላለማዊነት የሚደረግ ጉዞ መሆኑን ያስታውሰናል፣ ስለዚህ “ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን” (ዕብ 13፡14) የሚለውን በፍጹም ሳንዘነጋ ለእኛ የተሰጡን መክሊቶች ፍሬ እንዲያፈሩ ማደረግ ይኖርብናል። በዚህ አተያይ፣ እያንዳንዱ ጊዜ ውድ ይሆናል፣ ስለሆነም በእዚህ ምድር ላይ በምንኖርበት ወቅት ሁሉ ለሰማይ ቤት ያለንን ከፍተኛ ናፍቆት በመግለጽ ልንኖር ይገባናል፣ እግሮቻችንን በእዚህ ምድር ላይ በማደረግ፣ በእዚህ ምድር ላይ በመጓዝ፣ በእዚህ ምድር ላይ ሆነን በመሥራት፣ በእዚህ ምድር ላይ ሆነን መልካም የሚባሉ ተግባራትን በማከናወን፣ ልባችን እና አእምሮዋችን የሰማይ ቤትን እንዲናፍቁ ማደረግ ይኖርብናል።
ይህ ታላቅ ደስታ ምንን እንደሚያካትት በትክክል መረዳት አንችልም፣ ሆኖም ኢየሱስ ጌታቸው በተመለሰበት ሰዓት እና ወቅት ነቅተው ያገኛቸውን አገልጋዮቹን “እውነት እላችኋለሁ፤ ጌታቸውም በአጭር ይታጠቃል፤ በማእድ ያስቀምጣቸዋል፤ ቀርቦም ያስተናግዳቸዋል” (ሉቃ 12፡37) ብሎ ጌታው የተናገረው ቃል በእኛም ላይ እንደ ሚተገበር ለመገመት ይቻላል። የሰማይ ቤት ዘላለማዊ ደስታ በዚህ መንገድ ይገለጣል፦ ሁኔታው ወደ ጌትነት ይቀየራል፣ እናም አገልጋይ የሚባል ሰው አይኖርም፣ እግዚአብሔር እኛን ለማገልገል ራሱን ለእኛ ያቀርባል። አሁን ኢየሱስ ለእኛ እያደረገ የሚገኘው ጉዳይ ይህ ነው፣ ኢየሱስ ስለ እኛ ይጸልያል፣ ኢየሱስ ወደ እኛ ይመለከታል፣ ስለእኛ ወደ አባቱ ጸሎቱን ያቀርባል፣ ኢየሱስ አሁንም ቢሆን እኛን እያገለገለን ይገኛል፣ እርሱ የእኛ አገልጋይ ነው። እናም ይህ ትክክለኛ ደስታ ይሆናል። በመጨረሻው ዘመን በምህረት ከተሞላው ከእግዚኣብሔር ጋር መገናኘታችንን ማሰቡ በራሱ በተስፋ ይሞላናል፣ ንጹህ እና ነቀፋ የሌለብን ሆነን ለመገኘት ቀጣይነት ባለው መልኩ እንድንተጋ ያነሳሳናል። የበለጠ በፍትሐዊነት እና በወንድማማችነት መንፈስ የተሞላ ዓለም እንድንገነባ ያነሳሳናል።
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ!
በተጨማሪም በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ሕይወታችን የሆነውን ሀብት እንዴት መጠቀም እንደሚገባን እንድናስብ ጋብዞናል (ሉቃስ 12፡32-48)። “ያላችሁን ሽጡ፤ ምጽዋትም ስጡ፤ ሌባ በማይቀርብበት ብልም በማያጠፋበት በሰማያት የማያልቅ መዝገብ የሚሆኑትን የማያረጁትንም ኮረጆዎች ለራሳችሁ አድርጉ" (ሉቃስ 12፡33) ይላል።
እግዚአብሔር የሰጠንን ስጦታዎች ለራሳችን ብቻ ጠብቀን እንዳንይዝ ይልቁንም ለሌሎች በተለይም የእኛን እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በልግስና እንድንሰጥ ይመክረናል። ያለንን ቁሳዊ እቃዎች መጋራት ብቻ ሳይሆን ክህሎታችንን፣ ጊዜያችንን፣ ፍቅራችንን፣ መገኘትን እና ርህራሄን ለሌሎች አገልግሎት መስጠት ነው። ባጭሩ፣ እያንዳንዳችንን በዋጋ ሊተመን የማይችል እና የማይደገም መልካም፣ ሕያው ንብረት የሚያደርገን በእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ማልማት እና ለማደግ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ መደረግ አለበት። ያለበለዚያ እነዚህ ስጦታዎች ይደርቃሉ እና ዋጋቸው ይቀንሳል፣ ወይም እንደ ሌባ የሚነጥቀው በቀላሉ የሚበላ ነገር አድርገው የሚወስዱት ይሆናሉ።
እኛ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ነን፣ የእግዚአብሔር ስጦታ ደግሞ በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። ወደ ሙላት ለመምጣት እና ራሳችንን ለመግለጽ ቦታ፣ ነፃነት እና ግንኙነቶች እንፈልጋለን። ሁሉንም የህልውናችንን ገፅታዎች የሚቀይር እና የሚያጎናጽፍ ፍቅር እንፈልጋለን። ኢየሱስ እነዚህን ቃላቶች የተናገረው ወደ እየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ ሳለ፣ ራሱን በመስቀል ላይ ለደህንነታችን በሚያቀርብበት ወቅት ያለምክንያት የተናገራቸው ቃላት አይደሉም።
የምሕረት ሥራዎች የመኖራችንን ሀብት አደራ የምንሰጥበት እጅግ አስተማማኝ እና ትርፋማ ባንክ ናቸው፤ ምክንያቱም በዚያ፣ ወንጌሉ እንደሚያስተምረን፣ “በሁለት ትናንሽ የመዳብ ሳንቲሞች” ድሃዋ መበለት እንኳ በዓለም ላይ እጅግ ባለጸጋ ትሆናለች (ማር. 12፡41-44)።
በዚህ ረገድ ቅዱስ አውግስጢኖስ እንዲህ ይላል፡- “አንድ የመዳብ ሳንቲም ሰጥተህ አንድ የብር ሳንቲም ከተቀበልክ እና አንድ የወርቅ ሳንቲም ከተቀበልክ በዕድልህ ደስ ይልሃል፤ የሰጠኸው ነገር በእርግጥ ይለወጣል፤ ወርቅ ሳይሆን ብር ሳይሆን የዘላለም ሕይወት ወደ አንተ ይመጣል” ይላል። እናም ለምን እንደሆነ ያብራራል፦ "እሱ ይለወጣል፣ ምክንያቱም አንተ ራስህ ትለወጣለህ" በማለት ተናግሯል።
በዚህ ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት ልጆቿን የምታቅፍ እናት ማሰብ እንችላለን፡ በዓለም ላይ ካሉት ሁሉ በጣም ቆንጆ እና ባለጸጋ አይደለችምን? ወይም የወንድ ጓደኛ እና የሴት ጓደኛ አብረው ሲሆኑ እንደ ንጉስ እና ንግሥት እንደ ሆኑ አይሰማቸውምን? ሌሎች ብዙ ምሳሌዎችን ልናስብ እንችላለን።
ስለዚህ፣ የትም ብንሆን፣ በቤተሰብ፣ በደብራችን፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ፣ በፍቅር ለመንቀሳቀስ ማንኛውም ዕድል እንዳያመልጠን መሞከር አለብን። ይህ ኢየሱስ ከእኛ የሚጠይቀው የንቃት ዓይነት ነው፡ እርስ በእርሳችን የመተሳሰብ፣ ዝግጁ እና ተቆርቋሪ የመሆን ልማዳችንን እንድናሳድግ፣ እርሱ ከእኛ ጋር በእያንዳንዱ ጊዜ አብሮን ይጓዛል።
እህቶቼ እና ወንድሞቼ፣ ይህንን ፍላጎት እና ኃላፊነት ለማርያም አደራ እንስጥ፡ እሷ የማለዳ ኮከብ፣ ብዙ መለያየት በሚታይበት አለም የምሕረት እና የሰላም ጠባቂዎች እንድንሆን ትርዳን።
የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ (ላዛሪስት) ቫቲካን