ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ ለእግዚአብሔር የአንድነት ግብዣ መልካም ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ጥቅምት 4/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለጸሎት ተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች በዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባቀረቡት ስብከት፥ ለእግዚአብሔር የደስታ እና የኅብረት ግብዣ መልካም ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አሳስበዋል። ክቡራት ክቡራን አድማጮቻችን፥ ቅዱስነታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን በዕለቱ በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ያቀረቡትን ስብከት ትርጉም ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ለልጁ የሠርግ ግብዣን ስላዘጋጀ ንጉሥ ይነግረናል። (ማቴ 22፡1-14)። ይህ ንጉሥ ኃያል ሰው ነበር። ከሁሉም በላይ ደስታውን ከሌሎች ጋር ለመካፈል በመፈለጉ ሰዎችን ወደ ሠርጉ ዝግጅት የጋበዘ ለጋስ አባት ነው። ምንም እንኳን ይህን ማድረጉ ግብዣውን እንዳይቀበሉ ቢያደርገውም፥ ነገር ግን ማንንም ሳያስገድድ ሁሉን በመጋበዙ የልቡን መልካምነት ገልጧል። ንጉሡ ከሌሎች ሰዎች ጋር ለመገናኘት እና በዓሉን በኅብረት ለማክበር ነፃ ዕድል መስጠቱን እናስተውል። እግዚአብሔርም ይህን የመሰለ ግብዣ ያዘጋጅልናል። ከእርሱ ጋር እና እርስ በርሳችን የምንገናኝበትን አጋጣሚ ያዘጋጅልናል። በዚህ መሠረት እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር እንግዶች ነን። ነገር ግን ወደ ግብዣው መምጣት የእኛን ፈቃደኝነት እና ተሳትፎን ይጠይቃል። እግዚአብሔር በግብዣው እንድንገኝለት ይፈልጋል። ይህን የሚያደርገው በግድ ሳይሆን በነጻነት እንድንፈጽመው ይፈልጋል።

እግዚአብሔር የሚሰጠን የግንኙነት ዓይነትም ይህ ነው፥ ከእርሱ ጋር እንድንሆን ይጠራናል፣ ግብዣውን የመቀበል ወይም ያለመቀበል ዕድልም ሰጥቶናል። በእርሱ ሥር በግድ እንድንገዛ ሳይሆን ነገር ግን በአባትነት እና በልጅነት መንገድ እንድንገዛለት ይፈልጋል። ይህን የምናደርገው በግድ ሳይሆን በእኛ ነፃ ስምምነት ነው። እግዚአብሔር ነፃነትን እጅግ ያከብራል። ቅዱስ አጎስጢኖስ ይህን በማስመልከት ሲናገር፥ “ያላንተ ፈቃድ የፈጠረህ አምላክ ያለ አንተ ፈቃድ ሊያድነህ አይችልም” በማለት እጅግ በሚያምር አገላለጽ ተናግሮታል። (ከስብከቱ ቁ. 13)። እርግጠኛ የመሆን ችሎታ ስለሌለው ወይም ሁሉን ቻይ ባለመሆኑ ሳይሆን፥ ነገር ግን እርሱ እራሱ ፍቅር በመሆኑ ነፃነታችንን ሙሉ በሙሉ ያከብራል። በግድ ሳይሆን በነጻነት እንድንቀበለው ራሱን ለእኛ አቅርቦልናል።

ይህን መሠረት በማድረግ  ወደ ምሳሌው እንመለስ፥ ምሳሌውም እንዲህ ይላል፥ ‘ንጉሡ እንግዶቹን ወደ ሠርጉ እንዲጠሩ በማለት አገልጋዮቹን ላከ። ነገር ግን የተጋበዙት ሊመጡ አልፈለጉም’ (ማቴ 22፡3). የታሪኩ ድራማ የሚጀምረው ‘የእግዚአብሔርን ግብዣ አልቀበልም’ በማለት ነው። ነገር ግን ሰዎች የእግዚአብሔርን ግብዣ የማይቀበሉት ለምንድነው? ምናልባት ያልተደሰቱበት ግብዣ ነበር? አይደለም። ነገር ግን ቅዱስ ወንጌል እንዲህ ይለናል፥ ‘ለግብዣው ዋጋ ስላልሰጡ ወይም ግድ ስለሌላቸው አንዳንዶቹ ወደ እርሻቸው፥ ሌሎቹ ደግሞ ወደ ሥራቸው ሄዱ።’ (ማቴ 22፡ቁ. 5) ስለራሳቸው ነገር ስለሚያስቡ ግድ አልነበራቸውም። አባት እና ጌታ የሆነው ያ ንጉሥ ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ተስፋ ሳይቆርጥ መጋበዙን ይቀጥላል። በእርግጥ ግብዣውን የሚቀበል ሰው እስኪያገኝ ድረስ፥ ወደ ድሆችም ዘንድ ግብዣውን ያሰፋዋል። ከእነርሱ መካከልም ብዙ ነገረ እንደሌላቸው የሚያውቁ በርካታ ሰዎች አዳራሹ እስኪሞላ ወደ ግብዣው ይመጣሉ። (ማቴ 22፡8-10)

ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ስለ ራሳችን ጉዳይ ስናስብ ከርምርን፣ በእነርሱ በመጠመድ ለእግዚአብሔር ግብዣ ስንት ጊዜ ትኩረት ሳንሰጥ ቀርተናል! ብዙውን ጊዜ ትግላችን የራሳችንን ነፃ ጊዜ ለማግኘት ነው። ዛሬ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፃ የሚያወጣንን ጊዜ እንድናገኝ ይጋብዘናል። ለእግዚአብሔር የምናውልበት፣ ልባችንን የሚያበራ እና የሚፈውስ፣ በውስጣችን ሰላምን የሚሰጥ፣ መተማመን እና ደስታን የሚጨምር፣ ከክፉ ነገር የሚጥብቅ፣ ከብቸኝነት እና ከትርጉም የለሽ ሕይወት የሚያወጣን፣ ዘወትር ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበት ጊዜ እንዲኖረን ይፈልጋል። በሕይወታችን ውስጥ ለእግዚአብሔር ቦታ መስጠት መልካም ነው፤ ዋጋም አለው።

ለእግዚአብሔር ቦታ የምንሰጠው የት ነው? በመስዋዕተ ቅዳሴ ጊዜ፣ ቃሉን በመስማት፣ በጸሎት እና በበጎ ሥራ ወቅት፣ ደካሞችን ወይም ድሆችን በመርዳት፣ ብቸኝነት ወዳጠቃቸው ሰዎች ዘንድ በመቅረብ፣ ትኩረት የሚሹትን በማዳመጥ፣ የሚሠቃዩትን በማጽናናት እና አብሮ በመሆን ለእግዚአብሔር ቦታ እንሰጣለን። ነገር ግን ብዙዎች እነዚህ ነገሮች ጊዜን ማባከን እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ስለዚህም እራሳቸውን በግል ዓለም ውስጥ ዘግተው ይቀመጣሉ። ይህ ደግሞ ልባቸው ውስጥ ሐዘንን ይፈጥራል።

እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ፥ ለእግዚአብሔር ግብዣዎች ምላሽ የምሰጠው እንዴት ነው? በሕይወቴ ውስጥ ለእግዚአብሔር ምን ያህል ቦታ እሰጠዋለሁ? ሕይወቴ የሚመካው በግል ሥራዬ እና በትርፍ ጊዜዬ ላይ ነው ወይንስ ለእግዚአብሔር እና ለወንድሞቼ ባለኝ ፍቅር በተለይም በጣም በተቸገሩት ላይ ነው? ከእርሱ የሚመጣውን ሁሉ በትህትና ተቀብላ ለእግዚአብሔር ቦታ የሰጠች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እኛም የእርሱን ጥሪ እንድንሰማ ትርዳን።”

 

16 October 2023, 17:15

የገብርኤል ብሥራት ጥንታዊ መሠርት የያዘና የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት መልኣከ እግዚኣብሔር የሚለውን ስያሜ ያገኝው ከጸሎቱ ከመጀመሪያ ስንኝ የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት ከሚለው የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ስለ ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ይናገራል። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መሓል ጸጋን የተሞላሽ የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በበዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ።በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ የሚዘክረውን “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

መልኣኩ ገብርኤል ማሪያምን አበሰራት የሚለው የቀርብ ጊዜ ጸሎት

ሁሉንም ያንብቡ >