ር.ሊ.ጳ ሊዮ እግዚአብሔር መስቀልን ወደ ሕይወት መንገድ ይለውጠዋል ማለታቸው ተገለጸ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ ተከታተሉን።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም በቅድስት እሌኒ አማካይነት የመስቀሉ እንጨት መገኘቱን እና በንጉሠ ነገሥት ሄራክሌዎስ ወደ ቅድስት ከተማ የተመለሰውን ንዋያተ ቅድሳት በማሰብ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል ክብረ በዓልን ታከብራለች።
ግን ዛሬ ይህንን በዓል ማክበር ለእኛ ምን ትርጉም አለው? በመስዋዕተ ቅዳሴ ጊዜ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ይህንን እንድንረዳ ያስችለናል (ዮሐንስ 3፡13-17 ተመልከት)። ትዕይንቱ የተከናወነው በሌሊት ነው፡ ከአይሁድ መሪዎች አንዱ የሆነው ኒቆዲሞስ፣ ቅን እና አእምሮ ያለው ሰው (ዮሐንስ 7፡50-51 ተመልከት)፣ ኢየሱስን ሊገናኘው መጣ። ብርሃንን ፣ ምሪትን ይፈልጋል፡ እግዚአብሔርን ፈልጎ የናዝሬትን ጌታ እርዳታ ጠየቀ፣ ምክንያቱም እርሱ አስደናቂ ምልክቶችን የሚያደርግ ነቢይ መሆኑን ያውቃልና።
ጌታ ተቀብሎታል፣ ያዳምጠዋል፣ በመጨረሻም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ” የሰው ልጅ ተሰቃይቶ ሞቶ፣ ከሞት መነሳት እንዳለበት ገለጠለት (ዮሐ. 3፡15)። አክሎም፡- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና" (ዩሐ 3፡16) በማለት ይናገራል። ምናልባት በአሁኑ ጊዜ የእነዚህን ቃላት ትርጉም ሙሉ በሙሉ ያልተረዳው ኒቆዲሞስ፣ ከስቅለቱ በኋላ፣ የአዳኙን አካል ለመቅበር በሚረዳበት ጊዜ በእርግጠኝነት ሊረዳው ይችላል (ዮሐ. 19፡39)። እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለመቤዠት ሰው ሆኖ በመስቀል ላይ እንደሞተ ይረዳል።
ኢየሱስ ስለዚህ ጉዳይ ለኒቆዲሞስ የነገረው ከብሉይ ኪዳን የተነገረውን ታሪክ በማስታወስ ነው (ዘኁ. 21፡4-9)፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ በመርዛማ እባቦች ተነድፈው ሲመቱ፣ ሙሴ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመቀበል በሰራው እና በእንጨት ላይ ያስቀመጠውን የነሐስ እባብ በመመልከት ድነዋል።
እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ በመግለጥ አዳነን፣ ራሱን አጋር፣ መምህራችን፣ ሀኪም፣ ወዳጃችን አድርጎ በማቅረብ፣ ለእኛ እንኳን በቅዱስ ቁርባን የተሰበረ እንጀራ ሆነ። ይህንንም ሥራ ለመፈጸም፣ ሰው ከፈጠራቸው ጨካኝ የሞት መሣሪያዎች አንዱን ማለትም መስቀልን ተጠቅሟል።
ዛሬ “መስቀልን” ከፍ ከፍ አድርገን የምናከብረው በዚህ ምክንያት ነው፣ እግዚአብሔር ለእኛ መዳን ሲል ተሸክሞ ከሞት መንገድ ወደ ሕይወት መሣሪያነት ለወጠው፣ ከእርሱም ምንም ሊለየን እንደማይችል ያስተማረን ታላቅ ፍቅር ነውና (ሮሜ 8፡35-39) እናም የእርሱ ፍቅር ከኃጢአታችን የላቀ ነው።
እንግዲያውስ ከልጇ ጎን በቀራንዮ ያለች እናት በማርያም አማላጅነት የእርሱ የማዳን ፍቅሩ ሥር ሰዶ በውስጣችን ያድግ ዘንድ እኛም እርሱ እንዳደረገው እርስ በርሳችን እንዴት አንዳችን ለአንዳችን መሰጣጣት እንችል እናውቅ ዘንድ እርሷ በአማላጅነቷ ትርዳን።