ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሊዮ 14ኛ፥ ምዕመናን የሚስዮናዊነት ጥሪያቸውን እንደገና እንዲገነዘቡት አበረታቱ
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ ዛሬ ዓለም አቀፍ የሚስዮናውያን እና የስደተኞች ኢዮቤልዩን በማክበር ላይ እንገናኛለን። የወንጌልን ደስታ እና መጽናናት ለሁሉም ሰው በተለይም ሕይወታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ለሚገኝ ሰዎች ለማድረስ ካለው ፍላጎት የተነሳ ስለ ሚሲዮናዊ ጥሪያችን ያለንን ግንዛቤ ለማደስ ጥሩ አጋጣሚ ነው። በተለይ አገራቸውን ጥለው፣ ከሚወዷቸው ቤተሰቦች ርቀው በፍርሃት እና በብቸኝነት ሌት ተቀን የሚኖሩ፣ መድሎ እና ጥቃት የሚደርስባቸውን ስደተኛ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አስባለው።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በተቀበረበት በዚህ ቦታ የምንገኝበት ምክንያት፣ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት፥ እያንዳንዳችን በደስታ መናገር በምንችልበት፥ መላዋ ቤተ ክርስቲያን ሚስዮናዊት በመሆኗ በሁሉም ቦታ፣ በማንኛውም አጋጣሚ ሳታቅማማ እና ሳትፈራ ለሁሉም ሰው ወንጌልን ለመስበክ የመውጣት አስቸኳይነት በመኖሩ ነው። (የወንጌል ደስታ “Evangelii Gaudium” ሐዋርያዊ ማሳሰቢያ)።
አንዳንዴ በጦርነት፣ በፍትህ እጦት እና በመከራ ውስጥ በሚገኝ ዓለማችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ በዓለም ዳርቻዎች እንድንቀጥል መንፈስ ቅዱስ ይልክልናል። በጨለማ ትዕይንቶች መካከል፣ በታሪክ ብዙ ጊዜ እንደምንሰማው፥ ‘ጌታ ሆይ ለምን ጣልቃ አትገባም? ለምን የሌለህ ትመስለናለህ?’ በማለት ወደ እግዚአብሔር ሲነሳ የነበረው ጩኸት ዛሬም እንደገና ይነሳል።
ይህ የሥቃይ ጩኸት በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ላይ የሚታየው የጸሎት ዓይነት ሲሆን፥ ዛሬ ማለዳ ከነቢዩ ዕንባቆም መጽሐፍ ሰምተናል፥ ‘ጌታ ሆይ እኔ ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ‘ግፍ’ ብዬ ወደ አንተ እጮኻለሁ አንተም አታድንም። ክፉ ሥራ ለምን አሳየኸኝ? ጠማምነትንስ ስለ ምን ትመለከታለህ? ጥፋት እና ግፍ በፊቴ ነው፤ ጠብ እና ክርክር ይነሳሉ።’ (ዕብ. 1:2-3)
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ በኦሽዊትዝ ካደረጉት ታሪካዊ ጉብኝታቸው በኋላ ባቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በጭብጡ ላይ በማሰላሰል እንዲህ ብለዋል፥ ‘እግዚአብሔር ዝም ይላል፣ ነገር ግን ይህ ዝምታ ያለማቋረጥ የሚጸልይ ሰው ነፍስ መልስ የሚያገኝበት እና እንባውንም የሚጠርግ ነው’።
የእግዚአሔር ምላሽ ተስፋን ይከፍትልናል። ነቢዩ ያሸነፈ የሚመስለውን የማያመልጠውን የክፋት ኃይል ካወገዘ፥ እግዚአብሔር በበኩሉ ይህ ሁሉ ፍጻሜ እንደሚኖረው እና የጊዜ ገደብ እንደሚኖረው አስታውቋል። ምክንያቱም መዳን ይመጣል እንጂ አይዘገይም። ‘እርሱ ኮርቶአል ነፍሱ በውስጡ ቅን አይደለችም፤ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል’ (ዕብ 2፡4)። ስለዚህም ከእምነት የሚገኝ አዲስ የሕይወት እና የመዳን ዕድል አለ። ምክንያቱም ይህ አዲስ ሕይወት በመልካም በመጽናት ክፉን እንድንቋቋም የሚረዳን ብቻ ሳይሆን ሕልውናችንን የሚቀይር፥ እግዚአብሔር ዛሬም በዓለም ላይ ሊሠራ የሚፈልገውን የመዳን መንገድ የሚከፍትልንን የፍቅር ኃይል ስለሚሸከም ነው። እምነት ራሱን በኃይል አይጫንም። የማይታሰቡ ነገሮችን ለማድረግ የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት በቂ ነው። ‘የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ሾላ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል፤’ ብትሉት ይታዘዝላችሁ ነበር’ (ሉቃ. 17፡6)
ራሳችንን በወንጌል ርኅራኄ ውስጥ አድርገን ለጎረቤቶቻችን ስቃይ ስንጨነቅ የሚመጣ ድነት ነው። ውጤታማ የማይሆን በሚመስል መልኩ በዕለት ተዕለት ተግባራችን እና ቃሎቻችን ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገራት ትንሽ ዘር ዓይነት መዳን ነው። እራሳችንን ‘የማንጠቅም አገልጋዮች’ ስናደርግ ቀስ በቀስ የሚያድግ መዳን ነው። ማለትም የራሳችንን ምኞት ሳንፈልግ የእግዚአብሔርን ፍቅር ወደ ዓለም ለማምጣት፣ እራሳችንን ለቅዱስ ወንጌል፣ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን አገልግሎት ስናቀርብ ብቻ የሚገኝ ነው።
በዚህ እምነት የሚስዮናዊነት ጥሪያችን እሳት በውስጣችን እንድናቀጣጥል ተጠርተናል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደተናገሩት፥ ‘ከዚህ በፊት በሰው ልጅ የታሪክ ዘመን በእውነት ታይቶ በማይታወቅ የዕድገት ከፍታ፣ ጥልቅ ግራ መጋባት እና ተስፋ መቁረጥ በሚታይበት አስደናቂ ጊዜ ታጅበን ወንጌልን መስበክ የእኛ ፋንታ ነው።’ (የዓለም ተልዕኮ እሑድ ሰኔ 25 ቀን 1971 መልዕክት)።
ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ውስጥ አዲስ የሚስዮናዊነት ዘመን ተከፍቷል።
ለረጅም ጊዜ ‘ተልዕኮን’ ወንጌልን ሰምተው ወደማያውቁ ወይም በድህነት ውስጥ ወደሚገኙ ሩቅ አገሮች ከምናደርገው ጉዞ ጋር ስናገናኝ የቆየን ቢሆንም ዛሬ ‘ተልዕኮ’ በጂኦግራፊያዊ ድንበር የተገደበ አይደለም።ድህነት፣ ስቃይ እና ታላቅ ተስፋ የመሻት ፍላጎት ወደ እኛ እየመጣ ይገኛል። አመጽን እና ስቃይን ሸሽተው አደገኛ የባሕር ላይ ጉዞን የሚያደርጉ፣ አስተማማኝ ወደ ሆነ አካባቢ ለመድረስ ተስፋ የሚያደርጉ፣ ልዩነት እና አድሎአዊ መገለል ወደ ሌለበት ሥፍራ ለመድረስ የሚመኙ የበርካታ ስደተኛ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጩኸት፣ ስቃይ እና ተስፋ መቁረጥ እናያለን።
ለስብከተ ወንጌል ወደ ሩቅ አገራት ከምናደርገው ጉዞ ይበልጥ ተሰድደው ለሚመጡት በርኅራኄ በአብሮነት መንፈስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መስበክ ነው። በግለኝነት መንፈስ ተሞልተን ለራሳችንን መሸሸጊያ ከመፈልግ ይልቅ በሚደርስባቸው ስቃይ ምክንያት ከሩቅ አገራት በስደት የሚመጡትን በመመልከት፣ እጃችንን እና ልባችንን በመክፈት እንደ ወንድሞች እና እህቶች ተቀብለን ተስፋን እና መጽናናት ልንሰጣቸው ይገባል።
ስደተኞችን ለማገልገል እና በስደት ጉዳይ ላይ ከሚታይ ጭፍን የጥላቻ አመለካከት ባለፈ አዲስ የወንድማማችነት ባሕል ለማሳደግ የሚሠሩ በርካታ ሚስዮናውያን እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ምዕመናን አሉ። ነገር ግን ይህ ውድ አገልግሎት የእያንዳንዳችን አቅም ይፈትናል። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደተናገሩት፥ ‘ይህ ጊዜ እራሳችንን በቋሚ የተልዕኮ መንገድ የምንመሠርትበት ነው’ (የወንጌል ደስታ ሐዋርያዊ መልዕክት ቁ. 25)።
ይህ በሙሉ ቢያንስ ሁለት ታላላቅ የሚስዮናዊነት ቁርጠኝነቶችን ይጠይቃል። እነርሱም፥ ሚስዮናዊ ትብብር እና ሚስዮናዊ ጥሪ ናቸው።
በመጀመሪያ ደረጃ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል አዲስ የሚስዮናዊነት ትብብር እንዲበረታታ እጠይቃለሁ። እንደ ምዕራቡ ዓለም ያሉ ጥንታዊ የክርስትና ባህል ባላቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ፣ ከደቡቡ የዓለማችን ክፍሎች የመጡ ብዙ ወንድሞች እና እህቶች መገኘት ቤተ ክርስቲያንን የሚያድስ፣የበለጠ ግልፅ፣ ንቁ እና ክርስትናን የሚያነሳሳ የመለዋወጥ ዕድል ሆኖ መወሰድ አለበት። ከዚሁ ጋር ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሚስዮናዊ በሙሉ የሚያጋጥሙትን ባሕሎች በአክብሮት ተቀብሎ በመኖር ወደ መልካምነት እየመራ የወንጌልን ትንቢት እንዲያደርስ ተጠርቷል።
እንዲሁም የሚስዮናውያንነት ጥሪ ውበት እና አስፈላጊነት ለማስታወስ እፈልጋለሁ። በተለይ ይህን ለአውሮፓ ቤተ ክርስቲያን ስናገር፥ ዛሬ አዲስ የምእመናን፣ የገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም ቤተ ክኅነት የሚስዮናዊነት ግፊት አለ። በሚስዮን አገሮች አገልግሎታቸውን ለሚሰጡ ካህናት እና በተለይም በወጣቶች ዘንድ ጥሪን ሊቀሰቅስ የሚችል አዲስ ሃሳብ እና ልምድ እንዲኖር ያስፈልጋል።
ውድ ወንድሞቼ በየአገራቱ ለሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ሚሲዮናውያን እና ሚሲዮናውያት እንዲሁም ጥሪያቸውን በማስተዋል በማጤን ላይ ለሚገኙት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬዬን እልካለሁ። ለስደተኞችም ዘወትር መልካም አቀባበል አደርግላቸዋለሁ። የተሻገራችኋቸው ባሕሮች እና በረሃዎች በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ እንደተጻፈው፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን ራሱን ያቀረበበት ‘የመዳን ሥፍራዎች’ ናቸው። ይህን የእግዚአብሔርን ፊት በምታገኟቸው ሚስዮናውያን ውስጥ እንደምታገኙት ተስፋ አደርጋለሁ!
ኢየሱስን በማህፀኗ ተሸክማ ኤልሳቤጥን ለማገልገል ፈጥና ወደ ይሁዳ አገር ለሄደች እና የልጇ የመጀመሪያ ሚስዮናዊት ለሆነች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አደራ እሰጣለሁ። እያንዳንዳችን በኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት የፍቅር፣ የፍትሕ እና የሰላም ተባባሪዎች እንድንሆን ቅድስት ድንግል ማርያም ትደግፈን።”
