ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በብርሃነ ልደቱ ኮንሰርት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በብርሃነ ልደቱ ኮንሰርት ላይ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በብርሃነ ልደቱ ወቅት ሙዚቃ የነፍስ ማረፊያ ቦታ ሊሆን እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቫቲካን በተዘጋጀው የብርሃነ ልደቱ ኮንሰርት ላይ ከተሳተፉት አርቲስቶች እና አዘጋጆች ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለአርቲስቶቹ ባደረጉት ንግግር፥ የብርሃነ ልደቱ በዓሉ ወቅት እግዚአብሔር ትንንሽ በሆኑ የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ሊያገኘን እንደሚመጣ ያስታውሰናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቫቲካን ላለፉት 33 ዓመታት ያህል የብርሃነ ልደቱን ኮንሰርት በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ሲያቀርብ ቆይቷል። ዘንድሮ ቅዳሜ ታኅሳስ 4/2018 ዓ. ም. የቀረበው የብርሃነ ልደቱ ኮንሰትር ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ብዙም ሳይርቅ በሚገኘው አዳራሽ መዘጋጀቱ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከኮንሰርቱ አዘጋጆቹ እና አርቲስቶች ጋር ተገናኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ “መንፈሳዊ ሙዚቃ ከክርስቲያናዊ ጉዞአችን፣ ከትዝታዎቻችን እና ጥረቶቻችን ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን አስገንዝበው፥ የእያንዳንዱን ሰው ስሜት፣ ናፍቆት፣ ፍላጎት፣ ተስፋ እና ዳግም የመወለድ ታሪካችንን ቀላል በሆነ መንገድ በተመሳሳይ ጊዜ በጥልቀት የሚተርክ የቅርብ ጊዜ የጋራ ማስታወሻ ደብተር ነው” ብለዋል።


እግዚአብሔር በታሪኮቻችን ውስጥ ያገናኘናል

“የብርሃነ ልደቱ በዓል እግዚአብሔር ራሱን ለእኛ ለመግለጥ ሰብዓዊ የሕይወት አኗኗራችንን መምረጡን  ያስታውሰናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመቀጠልም፥ እግዚአብሔር ራሱን ለመግለጥ ትላልቅ ቦታዎችን የሚመርጥ ሳይሆን ነገር ግን ቀላል ሥፍራዎችን እንደሚመርጥ እና በትናንሽ ታሪኮቻችን ውስጥ ሊያገኘን የሚመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የዘንድሮ ዓመት ኮንሰርት ገቢ በኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፐብሊክ ውስጥ ለሚገኘው የሳሌዥያን ሚስዮናዊ ፕሮጀክት የሚሄድ መሆኑን አስታውሰው፥ እዚያም ለ350 ተማሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው እንዳመለከቱት፥ ይህ ፕሮጀክት እውነተኛ ውበት በራሱ ብቻ ተዘግቶ የሚቆይ ሳይሆን ነገር ግን ለዓለም ኃላፊነት የሚሰማቸውን ምርጫዎች ያስገኛል” ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አርተኛ፥ የብርሃነ ልደቱ በዓል እየቀረበ ባለበት በዚህ ወቅት ሙዚቃ የነፍስ መኖሪያ ቦታ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው፥ ልብ የሚናገርበት ውስጣዊ ቦታ፣ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን እና ሰብዓዊነታችን በፍቅሩ የበለጠ እንዲነሳሳ የሚያደርግ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

 

15 Dec 2025, 16:00