ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥  ዩክሬን ውስጥ በጦርነት የተገደሉትን በጸሎት ሲያስታውሱ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ ዩክሬን ውስጥ በጦርነት የተገደሉትን በጸሎት ሲያስታውሱ  

ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ፥ “እግዚአብሔር በዩክሬን ፍትሃዊ ሰላም እንዲያወርድ” በማለት ጸሎት አቀረቡ

በጦርነት በተጎዳችው ዩክሬን ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በኪየቭ ዩክሬይንን በማስታወስ ባደረሱት ጸሎት፥ የሁሉን ቻይ እግዚአብሔር በረከት እና ጥበቃ ለምነዋል። ብጹዕነታቸው ከዚህም በተጨማሪም በዩክሬን የነጻነት ቀን በዓልም ተገኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ባገሩ ቋንቋ ባደረሱት ጸሎት፥ ዩክሬን ውስጥ ፍትሃዊ ሰላም እንዲወርድ፣ እስረኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ፣ የታገቱት ሕጻናት ከወላጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ እና የጠፉትም እንዲገኙ፣ ሁሉም ሰው በሞት የተለዩዋቸውን እና የሚወዷቸውን ቤተሰቦች አስከሬን በማግኘት ሐዘናቸውን መግለጽ እንዲችሉ እና እያንዳንዳችን የሰላም ገንቢዎች የመሆን ድፍረት እና ጥበብ እንድናገኝ” በማለት ጸልየዋል።

ስብሰባዎች እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥረቶች

የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የዩክሬን ተልዕኮአቸውን በጀመሩበት ሦስተኛ ቀን ረቡዕ ሐምሌ 8/2018 ዓ. ም. ምሽት ወደ ኪየቭ ከመጓዛቸው በፊት የሊቪቭ ክልልን ጎብኝተዋል።

የብጹዕነታቸው ጉብኝ ዓላማ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለዩክሬን ያላቸውን ቅርበት ለመግለጽ እና ከነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተቀበሉት አደራ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. ባደረጉት የመጀመሪያ ተልዕኮአቸው ወቅት የጀመሯቸውን ግንኙነቶች፣ የቅድስት መንበር የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥረት እና የመገናኛ መንገዶች ለማጠናከር እንደሆነ ታውቋል።

ጥረቶቹ የሚያተኩሩት የጦር እስረኞችን ልውውጥ በማመቻቸት፣ ከዩክሬን በኃይል ወደ ሩሲያ እንደተወሰዱ የሚነገሩ ሕጻናትን መመለስ እና በግጭቱ ወቅት የተገደሉ ሰዎች አስከሬን ወደ አገራቸው መመለስ ላይ እንደ ሆነ ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በእነዚህ አካባቢዎች ከሚሠሩ የማኅበራት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ የያዙ ሲሆን፥ በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር ይፋዊ ስብሰባ ባያደርጉም ከሦስት ዓመታት በፊት መገናኘታቸው ይታወሳል።


የኪቫን ሩስ የጥምቀት ሥነ-ሥርዓት መታሰቢያ

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ረቡዕ ሐምሌ 8/2018 ዓ. ም. ጠዋት በሐዋርያዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቪስቫልዳስ ኩልቦካስ ባቀረቡት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ከተገኙ በኋላ የኪየቫን ሩስ የጥምቀት መታሰቢያን በማስመልከት የተጋጀውን ክብረ በዓል ተሳትፈዋል።

በኪየቭ በተካሄደ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተገኙት መካከል የተለያዩ የሃይማኖት ማኅበረሰቦች ተወካዮች፣ የዩክሬን-ግሪክ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ስቪያቶስላቭ ሼቭቹክ እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ይገኙበታል። ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን ጦርነቱ በሩስያ እና ዩክሬይን መካከል ከፈነዳበት ጊዜ ጀምሮ ዩክሬንን አሥራ አንድ ጊዜ ጉብኝተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከሌሎች የሐይማኖት መሪዎች ጋር
ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከሌሎች የሐይማኖት መሪዎች ጋር

የብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ጸሎት

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በኪየቭ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል አደባባይ የተዘጋጀውን ሥነ-ሥርዓት ላይ የተሳተፉ ሲሆን፥ እንደ ጣሊያኑ ዕለታዊ ጋዜጣ አቬኒር ዘገባ መሠረት፥ ሩስያ ሙሉ ወረራ ካደረገችበት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ አደባባዩ በጦርነቱ ለተገደሉት ሰዎች መታሰቢያ ሆኖ አገልግሏል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ከፕሬዚዳንት ዜለንስኪ እና ከሌሎች ተሳታፊዎች ጋር ሆነው፥ በጦርነቱ ወቅት የተገደሉት ሰዎች ፎቶግራፎችን በመመልከት በክብር ያስታወሷቸው ሲሆን፥ ብጹዕነታቸው ለመታሰቢያነታቸው እንዲሆን በማለት ቀይ የጽጌረዳ አበባዎችን ይዘው ሲጓዙ ታይተዋል።

የቦሎኛ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ፍትሃዊ ሰላም እንዲሰፍን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ጸሎታቸውን በማቅረብ አማላጅነቱንም ለቅዱስ ቮሎዲሚር አደራ ሰጥተዋል። የቅዱሱን ስም የዩክሬን እና የሩስያ ፕሬዝዳንቶች እንደሚጋሩት ጠቅሰው፥ “ቅዱስ ቮሎዲሚር የሁለቱን መንግሥታት መሪዎች አእምሮን እና ልብን እንዲያበራ፣ የፍትህ እና የሰላም ጎዳናዎችን እንዲከፍት” በማለት ጸሎት አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሊቪቭ
ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በሊቪቭ

በሊቪቭ የተደረጉ ስብሰባዎች

የብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ የሰላም ጸሎት በዩክሬን የጀመሯቸውን የቀድሞ ቀናት መርሃ ግብርንም ያካተተ ሲሆን፥ ይህም በመጀመሪያ ቀን ጉብኝታቸው በፖላንድ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው በዛኪድ-1 የጦር እስረኞችን የጎበኙበት መሆኑ ይታወሳል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በኋላም በሊቪቭ የክልሉ ወታደራዊ አስተዳደር ኃላፊ ከሆኑት ማክሲም ኮዚትስኪን ጋር የተገናኙ ሲሆን፥ ኃላፊው ቅድስት መንበር የጦር እስረኞች እና ሕጻናት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስ እንዲሁም የጠፉትን ለማግኘት ላደረገችው ጥረት ካመሰገኑ በኋላ በሊቪቭ ክልል፣ በቅድስት መንበር እና በጣሊያን ተቋማት መካከል የትብብር መስኮች እንዲዘረጉ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ በቀኑ መጨረሻ በሊቪቭ የሚገኘውን የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበረሰብ ዋና ጽሕፈት ቤትን ጎብኝተው፥ ከድርጅቱ ዕርዳታን የሚያገኙ የውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከአካባቢው ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ አባላትን ባነጋገሯቸው ወቅት በሰጡት የማበረታቻ ቃል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ቅርበት ገልጸውላቸዋል።

 

16 Jul 2026, 11:14